Asset Publisher

null ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የጉምሩክ ኮሚሽን ከታህሳስ 18 እስከ 25/2016 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 404 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና 398 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የወጭ፤ በድምሩ 803 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተይዘዋል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣የመኪና መለዋወጫ፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡
በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የገቢ እና የወጭ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር አዲስ አበባ ኤርፖርት፣ አዋሽ እና ድሬደዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ በቅደም ተከተላቸውም 254 ሚሊዮን፣ 213 ሚሊዮን እና 132 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ ችለዋል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ ሲሆን ኮንትሮባንዱን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 12 ተጠርጣሪዎች እና ሰባት ተሽከርካሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የህግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች ፣ የክልልና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለመላው ህዝባችን ምስጋናውን ያደርሳል፡፡

የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጉምሩክ ኮሚሽን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ጉምሩክ ኮሚሽንን የተመለከቱ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/ecczena
በድረ ገጽ፦ www.ecc.gov.et
በቴሌግራም፦ https://t.me/EthiopianCustomsCommission