የናይጀሪያ መንግስት ልኡካን ቡድን በጉምሩክ ኮሚሽን የልምድ ልውውጥ እና ጉብኝት አካሄዱ
የናይጀሪያ መንግስት ልኡካን ቡድን በጉምሩክ ኮሚሽን የልምድ ልውውጥ እና ጉብኝት አካሄዱ
**********************
የናይጀሪያ ጉምሩክ አገልግሎትን ጨምሮ ከተለያዩ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች የተወጣጡ የልኡካን ቡድን አባላት በጉምሩክ ኮሚሽን በመገኘት የልምድ ልውውጥ ያካሄዱ ሲሆን የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን የስራ እንቅስቃሴም ተመልክተዋል፡፡
የልኡካን ቡድኑ በጉምሩክ ኮሚሽን አገልግሎቱን ዘመናዊ እና ቀልጣፋ ለማድረግ የተሰሩት ስራዎች አበረታች እና ተጨባጭ ልምድ ያገኙበት መሆኑን ጠቁመው በዋናው መስሪ ቤት እና በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የስራ ከባቢን ምቹና ማራኪ ለማድረግ የተሰራው ስራም በተሞክሮነት የሚወስዱት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የልኡካን ቡድኑ አክለውም፣ ኮሚሽኑ ወረቀት አልባ አገልግሎትን በመተግበሩ ለደንበኞች በየትኛውም ሁኔታ እና ጊዜ አግልግሎት እንዲያገኙ መደረጉ፣ ኮሚሽኑ በከፍተኛ የለውጥ ግስጋሴ ላይ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የናይጀሪያ መንግስት ልኡካን ቡድን በሁለት ቀን ቆይታቸው የአዲስ አበባ ኤርፖርት እና በሞጆ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤትን የጎበኙ ሲሆን የልምድ ልውውጡ ተግባራዊ የሆኑ እውቀቶችን የቀሰሙበት እና ስኬታማ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን የኮሚሽኑ የለውጥ አማካሪ አቶ መንግስቱ ተፈራ በበኩላቸው፣ በኮሚሽኑ ባለፉት ሶስት ዓመታት መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸው በቀጣይም የአገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ የሚያዘመኑን ኮሚሽኑን ብቁ ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡