ኤክሳይዝ ታክስ የቅንጦት እቃዎች ሆነው ዋጋቸው ጨመረም አልጨመረም መሰረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ፍላጎታቸው በማይቀንስ ዕቃዎች ላይ፣ እንዲሁም የሕብረተሰቡን ጤንነት የሚጎዱና ማህበራዊ ችግር የሚያስከትሉ ዕቃዎችን አጠቃ በዓለማችን ለመጀመሪያ ጊዜ ኤክሳይዝ ታክስ የተጀመረው በእንግሊዝ ፓርላማ በ1643 ዓ.ም ሲሆን በወቅቱ የመንግስት ገቢን ከፍ ለማድረግ ታስቦ የተጣለ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በኢትዮጵያም ታክሱ ከረጅም ጊዜያት ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን የመንግስትን የገቢ አቅም በማሳደጉ ረገድ የበኩሉን ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ ኤክሳይዝ ታክስ የቅንጦት እቃዎች ሆነው ዋጋቸው ጨመረም አልጨመረም መሰረታዊ በመሆናቸው የገበያ ፍላጎታቸው በማይቀንስ ዕቃዎች ላይ እንዲሁም የሕብረተሰቡን ጤንነት በሚጎዱና ማህበራዊ ችግር የሚያስከትሉ ዕቃዎችን አጠቃቀም ለመቀነስ ሲባል የተጣለ ታክስ ነው፡፡ ታክሱ በአንዳንድ የተመረጡ ዕቃዎች ላይ ማለትም በሀገር ውስጥ በሚመረቱና ወደ አገር ውስጥ በሚገቡት ላይ ብቻ የሚጣል ነው፡፡ ኤክሳይዝ ታክስ አላማው ማህበራዊ ጠቀሜታ የሌላቸውን እና የህብረተሰቡን ጤንነት የሚጎዱ ምርቶችን መቀነስ፣ የቅንጦት የሆኑ የፍጆታ እቃዎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደር እና የመንግስትን ገቢ ማሳደግ ናቸው፡፡ የመንግስትን ገቢ ማሳደግ ሲባል የተሻለ ገቢ ያላቸው ሠዎች በሚጠቀሙባቸው እቃዎች እና የመግዛት ፍላጎታቸው በማይቀንስባቸው ምርቶች ላይ ታክሱን በመጣል ለአገር ተጨማሪ ገቢ ማስገኘት ነው፡፡ የቅንጦት እቃዎች ከሠው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት በላይ የሆኑ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ውድ የሆኑ መጠጦች፣ ሲጋራ፣ ሽቶና የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡ ይህ የታክስ ዓይነት ለህብረተሰቡ ጤንነት አደጋ የሆኑ የትምባሆ እና ሌሎች ምርቶች ላይ ዋጋቸው እንዲጨምርና የተጠቃሚዎቹ ቁጥር እንዲቀንስ ታስቦ የሚጣልም ነው፡፡ በተጨማሪም የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት እንዲሁም ከውጪ የሚገቡ እቃዎች ሀገር ውስጥ የተመረቱትን ከገበያ ውጭ እንዳያደርጓቸው ታስቦ ይጣላል። ይህ ታክስ ከሚጣልባቸው እቃዎች ውስጥ አንዱ መኪና ነው፡፡ የግል አውቶሞቢል ላይ አምስት ዓይነት ቀረጥና ታክስ ይጣላል፡፡ እነሱም፡- የጉምሩክ ቀረጥ፣ ኤክሳይዝ ታክስ፣ ተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ሱር ታክስ እና ዊዝሆልዲንግ ታክስ ናቸው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት አምስቱ ታክሶች እያንዳንዳቸው የየራሳቸው የታክስ መጣኔ (tax rate) ያላቸው ሲሆን መጣኔዎቹ ከዚህ በታች በቀረበው ሠንጠረዥ ተመልክተዋል፡፡

ተ.ቁ የቀረጥና ታክስ ዓይነቶች መጣኔ በመቶኛ
1 የጉምሩክ ቀረጥ 35
2 ኤክሳይዝ ታክስ- የተሽከርካሪው ሲሊንደር አቅም (cyliderical capacity) እስከ 1300 ከሆነ 30
የተሽከርካሪው ሲሊንደር አቅም ከ1301 እስከ 1800 60
የተሽከርካሪው ሲሊንደር አቅም ከ1800 በላይ ከሆነ 100
3 ተጨማሪ እሴት ታክስ 15
4 ሱር ታክስ 10
5 ዊዝሆልዲንግ ታክስ 3
ለአዲስ የግል አውቶሞቢል የሚከፈለው ቀረጥና ታክስ የሚሰላው በአውቶሞቢሉ የቀረጥ ማስከፈያ ዋጋ ( Duty paying value) ላይ ተመርኩዞ ነው፡፡ የቀረጥ ማስከፈያ ዋጋ ለግል አውቶሞቢል የወጣው ወጪ ድምር ነው፡፡ ይህ ድምር አውቶሞቢል ለመግዛት (cost)፣ ለኢንሹራንስ (insurance)፣ እና ለማጓጓዝ (freight) እስከ ኢትዮጵያ ድንበር ድረስ የወጣውን ወጪ ያካትታል፡፡ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወደ ሀገራችን የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን የቀረጥ ማስከፈያ ዋጋ የሚያሳይ መረጃ (data) ያጠናቀረ ሲሆን አስመጪው የቀረበውን ወጪ ከዚሁ የመረጃ ቋት ጋር በማመሳከር በሚገኘው የቀረጥ ማስከፈያ ዋጋ መሰረት ተከፋዩ ቀረጥና ታክስ ይሰላል፡፡ ለምሳሌ፡- የቀረጥ ማስከፈያ ዋጋው ብር 70,000፣ የሲሊንደር አቅሙ 1280 የሆነ አዲስ ቶዮታ ኮሮላ አውቶሞቢል ቢገባ፤ ቀረጥና ታክሱን ለመወሰን የሚከተሉት አምስት የስሌት ደረጃዎች ይሰላሉ፡፡ የመጀመሪያው የጉምሩክ ቀረጥ ሲሆን ማስከፈያ ዋጋው በጉምሩክ ቀረጥ መጣኔ በማባዛት የሚሰላ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ተከፋዩ የጉምሩክ ቀረጥ 70,000 X 35/100 = 24,500 ይሆናል፡፡ በቀጣይ የሚሰላው ኤክሳይዝ ታክስ ሲሆን በዚህ ስሌት የአውቶሞቢሉን የቀረጥ ማስከፈያ ዋጋ እና ተከፋይ የጉምሩክ ቀረጥ በመደመር በኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔ ማባዛት ነው፡፡ በዚህ ስሌት መሰረት ተከፋዩ ኤክሳይዝ ታክስ መጠን (70,000 + 24,500) x 30% = 28,350 ይሆናል፡፡ በሶስተኛ ደረጃ የሚሰላው ተከፋይ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሲሆን በዚህ ስሌት የአውቶሞቢሉን የቀረጥ ማስከፈያ ዋጋ፣ ተከፋይ የጉምሩክ ቀረጥ እና ኤክሳይዝ ታክስ በመደመር በተጨማሪ እሴት ታክስ ሬት ይባዛል፡፡ በዚህ መሰረት የሚከፈለው ተጨማሪ እሴት ታክስ ብር (70,000 + 24,500 + 28,350) X 15% = 18,427.5 ይሆናል፡፡ በአራተኛ ደረጃ የሚሰላው ሱር ታክስ ሲሆን ስሌቱ የአውቶሞቢሉን የቀረጥ ማስከፈያ ዋጋ፣ ተከፋይ የጉምሩክ ቀረጥ፣ ኤክሳይዝ ታክስ እና ተጨማሪ እሴት በመደመር በሱር ታክስ መጣኔ ማባዛት ነው፡፡ በዚህ መሰረት የሚከፈለው ሱር ታክስ (70,000 + 24,500 + 28,350+ 18,427.5) X 10% = 14,127.75 ብር ይሆናል፡፡ በአምስተኛ ደረጃ ተከፋዩን ዊዝሆልዲንግ ታክስ ነው፡፡ ይህ ታክስ የሚሰላው የቀረጥ ማስከፈያ ዋጋን በዊዝሆልዲንግ ታክስ መጣኔ በማባዛት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ተከፋዩ የዊዝሆልዲንግ ታክስ 70000 x 3/100 = 2100.00 ብር ይሆናል፡፡ በመጨረሻው የስሌት ደረጃ ሁሉም ተከፋይ ቀረጥና ታክሶች ይደመራሉ፣ በዚህ መሰረት መንግስት ከአውቶሞቢሉ የሚሰበስበው ቀረጥና ታክስ ስሌት ድምር 24,500 + 28,350+ 18,427.5 + 14,127.75 + 21,000 = 87505.25 ብር ይሆናል:: በራሄል ወልዴ

Today 11 Yesterday 12 Week 64 Month 23 All 11209

Currently are 19 guests and no members online