ኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ በሀገር ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ሰፊና ተደራራቢ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ
(ጉምሩክ ኮሚሽን፣ ታህሳስ 22 ቀን 2016 ዓ.ም)
በጉምሩክ ኮሚሽን የተዘጋጀ ኮንትሮባድ እና ህገወጥ ንግድን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል የጸረ ኮንትሮባንድ የንቅናቄ መድረክ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ሲሆን በንቅናቄ መድረኩም የፌደራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
በንቅናቄ መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ፣ ኮሚሽኑ ኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸው ችግሩን በአግባቡ ለመከላከል የሚያስችሉ የህግ፣ የአሰራርና የአደረጃጀት ማሻሻያዎች መደረጋቸውንም አስረድተዋል፡፡
ኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ በሀገር ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ሰፊና ተደራራቢ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ ድርጊቱን ለመግታት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረው የንቅናቄ መድረኩ በተቋማት መካከል ያለውን ቅንጅታዊ ስራ ለማጠናከር የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
ኮሚሽነር ደበሌ አክለውም ኮንትሮባንድ፤ የንግድ ስርዓቱን በማዛባት፣ ገቢን በማሳጣት እና ኢንቨስትመንትን በማዳከም በሀገር ላይ ተደራራቢ ችግሮች የሚያስከትል መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የኮንትሮባንድ ወንጀል በሀገራችን ለሚከሰቱ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች አንዱ መንስኤ እየሆነ እንደሚገኝ ኮሚሽነር ደበሌ ገልጸው ችግሩ በኮሚሽኑ ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ በህግ ኃላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት እና መላው ህብረተሰብ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጉምሩክ ኮሚሽንን የተመለከቱ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/ecczena
በድረ ገጽ፦ www.ecc.gov.et
በቴሌግራም፦ https://t.me/EthiopianCustomsCommission